የቤተል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የዕምነት መግለጫ


1. ስያሜ

ይህ የዕምነት መግለጫ በቨርጂንያ ውስጥ አሌክሳንደርያ ከተማ የምትገኘው የቤተል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የዕምነት መግለጫ ተብሎ ይታወቃል።

2. ዓላማ

2.1. ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በእምነት እንዲቀበሉና የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲወርሱ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በሙላት መስበክና ማስተማር፡፡ 2ጢሞ4፡2

2.2. የክርስቲያኖች እምነትና ታማኝነት እንዲጠነክር በፀሎት፣ በእግዚአብሔር ቃልና በምክር የታነፀ ሕይወት አንዲኖራቸውና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታጥቀው በሕይወታቸው ጌታ ኢየሱስን እያንፀባረቁ እንዲኖሩ መደገፍ፡፡ ሐዋ 20፡20-21

2.3. ፀጋው ያላቸውን አገልጋዮች የእምነታቸውን ፍሬ በጥንቃቄ በመመልከት እንደየ ጥሪያቸው በአገልግሎት ማሰማራት፡፡ 1ጢሞ 5፡22

2.4. አማኞችን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ምሳሌ በመሆን ማሠልጠንና ማሰለፍ፡፡ 1ጢሞ 4፡11-13

2.5. አማኞችን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅና ደቀመዛሙርት ማድረግ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፣ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ብሎ ያዘዘውን ቃል በተግባር ማዋል፡፡ ማር 16፡15

2.6. የክርስቶስ አካል ከሆነችው ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ጋር መንፈሳዊ ሕብረትና አንድነት ማድረግ፡፡ ኤፌ1፡15-16

2.7. በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚከናወኑ ማኅበራዊ ነክ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍና ለቅዱሳን ሁሉ በሚደረግ አስፈላጊ እርዳታ በሙሉ ፈቃደኝነት መሳተፍ፡፡ ሐዋ 11፡29-30

3. መጽሃፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ- የብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍትና አዲስ ኪዳን 27 መጻሕፍት በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑንና በሰው እምነትና ሕይወት ላይ የመጨረሻ ሥልጣን ያለው የቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት እርሱ ብቻ እንደሆነ እናምናለን፡፡ 2ጢሞቴዎስ 3.16; ዕብራውያን 4.12 ፤ 2ኛጴጥ 1፣ 20-21::


የእምነት መግለጫ


3.1. እግዚአብሔር

3.2. እግዚአብሔር አብ

3.3. ዘለዓለማዊ ፣ የማይወሰን፣ ፍጹም፣ ራሱን በመንፈስ ቅዱስ በሚገልጥና ሁሉን በሚችል በሁሉ ቦታ በሚገኝ ሁሉን በሚያውቅ በማይለዋወጥ፣ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ ዘፍጥረት 1.1-31; ዘፍጥረት 2.7; 1ቆሮንቶስ 8.6; 2ቆሮንቶስ 6.18; 1ጢሞቴዎስ 1.17

3.4. ኢየሱስ ክርስቶስ

3.4.1. የእግዚአብሔር አብ ልጅ መሆኑን፣ በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን፣ ስለኃጢያታችን በመስቀል ላይ የተሰቃየና የሞተ የተቀበረ በሶስተኛውም ቀን ከሞት በአካል ተነስቶ ለሰዎች ተገልጦ በክብር ወደ ሰማይ ያረገ መሆኑን፣ አሁንም በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ዘወትር ለእኛ እንደሚማልድልን፣ ዳግመኛም በታላቅ ክብርና ሥልጣን እንደሚመለስ እናምላለን፡፡ ማቴዎስ 16.16፣ የሐዋሪያት ሥራ 5.30-31፣ ማቴዎስ 1.23፣ 1ቆሮንቶስ 15.3-8፣ የሐዋሪያት ሥራ 1.9-11

3.5 መንፈስ ቅዱስ

3.5.1. ፍፁም አምላክ፣ አጽናኝ፣ አስተማሪና ወደ እውነት የሚመራ መንፈሳዊ አባቶችን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን ያንቀሳቀሰና የመራ፣ በአማኞችም ውስጥ አድሮ መንፈሳዊ ስጦታዎችና ኃይልን በማከፋፈል ቤተክርስቲያንን እንደሚያንጽ፣ ዓለምንም ስለኃጢአት፣ ስለጽድቅና ስለፍርድ እንደሚወቅስ እናምናለን፡፡ የሐዋርያት ሥራ 2፣ 1-11; 2ጴጥሮስ 1.21; የሐዋሪያት ሥራ 1.8; 1ቆሮንቶስ 12.4-11; ኤፌሶን 4.11-12

3.5.2. አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚጠመቁ እናምናለን፡፡ ማርቆስ 16.17-18; የሐዋርያት ሥራ 10.44-46

3.5.3. በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 መሠረት ዛሬም አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳን መናገርን፤ በፀሎትና በእምነት ሊቀበሉት እንደሚገባ ከክርስቶስ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን እናምናለን፡፡ የሐዋርያት ሥራ 1.4-5፣ 2፣1-4፣ 2.38-39፣ ኤፌሶን 5.18

3.5.4. በሐዋርያት ዘመን እንደነበረ በዘመናችንም የመንፈስ ቅዱስ የፀጋ ስጦታዎች ለአማኞች እንደሚሰጥ እናምናለን፡፡ 1ቆሮንቶስ 12.1-11፣

3.5.5. በዚህም ዘመን በቤተክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስን በማክበር በአማኞች ውስጥ ሆኖ እንደሚሠራ እናምናለን፡፡ ዮሐንስ 16. 7-15

3.5.6 ስላሴ

3.5.7. በአካልና በስራ ሶስት በመለኮታዊ ባህሪና አምላክነቱ አንድ አምላክ መሆኑን እናምናለን።

3.6 አዲስ ፍጥረት (ድነት)
ሰው በመጀመሪያ ያለ ኃጢአት መፈጠሩን እናምናለን፡፡ ይሁን እንጂ አዳም በፈቃደኝነት ኃጢአት ላይ በመውደቁ ምክንያት ሰው ሁሉ የኃጢአት ባህሪ ይዞ መወለዱን እናምናለን:: ነገር ግን ስለ ሐጢያቱ ተጸጽቶና ንስሐ ገብቶ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኙና ጌታው አድርጎ የተቀበለ ሰው ሁሉ፤ ከመንፈስ ቅዱስና ከእግዚአብሔር ቃል የተወለደ አዲስ ፍጥረትና የእግዚአብሔር ልጅም መሆኑን እናምናለን፡፡ ዘፍጥረት 1.26-28፣ ዘፍጥረት 3.1-24፣ ሮሜ10.9-10፣ ዮሐንስ1.12-13

4.5. የውሃ ጥምቀት

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ መሠረት አማኝ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በውሃ እንደሚጠመቅ እናምናለን፡፡ማቴ 28:19

4.5.1. አንድ ክርስቲያን ለዚህ ዓለምና ለኃጢአት የሞተ፣ ለፅድቅ ደግሞ ህያው መሆኑን በእግዚአብሔርና በቅዱሳን ፊት የሚያረጋግጥበት ምሳሌያዊ ተግባር መሆኑን ታምናለች፣በዚሁም መሠረት የአዋቂ ጥምቀትን በተግባር ታውላለች፡፡ ሮሜ 6፡1-7፤ ማር16፡16

4.5.2. ቤተክርስቲያንዋ በምታዘጋጀው ትምሕርት መሠረት የውሃ ጥምቀት ይከናወናል።ሮሜ6፣1-7

4.6 ቅዱስ ቁርባን

4.6.1. በህብስትና በወይን ጭማቂ የሚዘጋጀውን ቅዱስ ቁርባን፣ የጌታችን የመድኃኒታችን ስቃይና ሞት የምናስብበትና ሞቱንም የምንናገርበት ቅዱስ ሥርዐት መሆኑንና ስለዚህም ጌታ እስኪመጣ ድረስ በቤተ ክርስቲያን መከናወን ያለበት መሆኑን እናምናለን፡፡ ማቴዎስ 26.26-28፣ 1ቆሮንቶስ 11. 23-30

4.7 ቅድስና

4.7.1. የክርስቲያኖች ጥሪ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝና በቅድስና ማለትም በእግዚአብሔር ቃል መሰረት የተለየና ከሃጢያት የፀዳ ሕይወትን በመለማመድ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራትና ምሳሌነት ያለው ህይወት በመኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከፍ ማድረግ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ኤፌሶን 2.10፣ 1ጴጥሮስ 1.15፣ 2ቆሮንቶስ 7.1፣ ዮሐንስ 15.1-11፣ 1ጢሞ4-12

4.8 የክርስቶስ ዳግም ምፅአት

4.8.1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር እንደገና እንደሚመጣ፣ በእርሱ አምነው የሞቱት ቀድመው እንደሚነሱ ሕያዋን የሆኑት ደግሞ እርሱን ለመቀበል እንደሚነጠቁ እናምናለን:: 1ቆሮንቶስ 15.51-52፣ 1ተሰሎንቄ 4.15-17

4.9 ፍርድ

4.9.1. ጻድቃን ከጌታ ጋር ለዘላለም እንደሚኖሩ ኃጢአተኞች ግን ከእግዚአብሔር ፊት ተለይተው በገሃነም እሳት ለዘላለም ተፈርዶባቸው እንደሚሰቃዩ እናምናለን፡፡ ራዕይ 7.9-15፣ 19.11-14፣ ሉቃስ 13.23-30፣ ማቴዎስ 25.31-46፣ ራዕይ 20.10-15፣ ማቴዎስ 24.38-44፣ 25.1-13፣ ፣ የሐንስ 14.2-4